ባለፈው ክፍል ላይ መለኮት የሆነው የእግዚአብሔር ልጅ በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር መልአክ በመባል ይገለጥ እንደነበር እና በዚህ መንገድ ከተገለጠባቸው አጋጣሚዎች አንዱ የሆነውን የጌዴዎንን ታሪክ ማየት ጀምረን ነበር። ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ለመግለጽ እንደሞከርነው መልአክ የሚለው ቃል በዕብራይስጥ "ማልአኽ/מַלְאַ֥ךְ" በግሪክ ደግሞ "አንጌሎስ/ἄγγελος" ሲሆን ትርጉሙ መልእክተኛ ማለት ነው። የመልእክተኝነት ግብር ያለው የትኛውም አካል መልአክ/መልእክተኛ ተብሎ ይጠራል። የመልእክተኛው ባህርይ ሰዋዊ ይሁን፥ የፍጡራን መናፍስት ይሁን መለኮታዊ ይሁን የሚታወቀው በአውዱ ነው። እንጂ አንድ አካል መልአክ ስለተባለ ብቻ ከፍጡራን መናፍስት አንዱ ነው ማለት አይደለም። የእግዚአብሔር ልጅም መልአክ የተባለው የአባቱ መልእክተኛ ስለነበር እንጂ ፍጡር ስለሆነ አይደለም።
እግዚአብሔር ቢፈቅድ ከባለፈው ክፍል በመቀጠል የእግዚአብሔር ልጅ ጌታ ኢየሱስ የእግዚአብሔር መልአክ በመባል ለጌዴዎን የተገለጠበትን ክስተት ማየት እንቀጥላለን፦
"ጌዴዎንም የእግዚአብሔር መልአክ እንደ ሆነ አየ፤ ጌዴዎንም። አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ #ወዮልኝ፤ የእግዚአብሔርን #መልአክ ፊት ለፊት #አይቻለሁና አለ" (መሳ 6:22)
ባለፉት ተከታይ ክፍሎች ጌዴዎን ለእግዚአብሔር መልአክ መሥዋዕት ማቅረብ እንደሚቻል ያወቀበትን የኦሪት ክፍል መመልከት ጀምረን ነበር። ይህ የኦሪት ክፍል ዘፍ 35:1 ሲሆን በዚያ ክፍል ላይ ያዕቆብ ወደ ቤቴል ሄዶ ከወንድሙ ከዔሳው በሸሸ ጊዜ ለተገለጠለት እግዚአብሔር መሠዊያ እንዲሰራ የታዘዘበት ታሪክ ተዘግቧል። ያዕቆብ ከወንድሙ ከዔሳው በሸሸ ጊዜ እግዚአብሔር ለእርሱ የተገለጠበትን ታሪክ የምናገኘው በዘፍ 28:11-19 ነው። እግዚአብሔር በሕልም ለያዕቆብ ይገለጥለታል (ዘፍ 28:12-13) ከተገለጠለት ድንጋይን ሐውልት አድርጎ ያቆመውና ዘይት ያፈስስበታል (ዘፍ 28:18) የዚያንም ቦታ ስም ቤቴል ብሎ ይጠራዋል (ዘፍ 28:19) ከዚያም በዚያ በቤቴል ለተገለጠለት እግዚአብሔር ስዕለትን ይሳላል (ዘፍ 28:20-22) ይህ ከሆነ ከረዥም ጊዜ በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ በሕልም ተገልጦ "ሐውልት የቀባህበት በዚያም ለእኔ ስዕለት የተሳልክበት የቤቴል አምላክ እኔ ነኝ" ይለዋል (ዘፍ 31:10-13) ይህ በዘፍ 28:11-22 ያዕቆብ ከወንድሙ ከዔሳው በሸሸ ጊዜ በቤቴል የተገለጠለት አምላክ የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን ያሳያል። ስለዚህ በዘፍ 35:1 ላይ "ተነስተህ ወደ ቤቴል ሂድ በዚያም ኑር፥ ከወንድምህ ከዔሳው በሸሸህ ጊዜ ለተገለጠልህ እግዚአብሔር መሠዊያ ስራ" ሲል ለእግዚአብሔር መልአክ መሠዊያ ስራ ማለት ነው።
በዘፍ 35:1 ላይ መሠዊያ እንዲሰራለት የታዘዘው እግዚአብሔር የእግዚአብሔር መልአክ ለመሆኑ ተጨማሪ ሰዋሰዋዊ (Grammatical) ማስረጃ አለ።
እንመልከተው፦
"እግዚአብሔርም ያዕቆብን አለው። ተነሥተህ ወደ ቤቴል ውጣ፥ በዚያም ኑር፤ ከወንድምህ ከዔሳው ፊት በሸሸህ ጊዜ ለተገለጠልህ #ለእግዚአብሔርም መሠውያውን አድርግ" (ዘፍ 35:1)
በዘፍ 35:1 ላይ "ከወንድምህ በሸሸህ ጊዜ ለተገለጠልህ እግዚአብሔር" በሚለው ሀረግ ውስጥ #እግዚአብሔር ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል "אֵל֙/ኤል" የሚለው ቃል ሲሆን (Strong's H410) አምላክ ማለት ነው። በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ ይህ ቃል በተደጋጋሚ ለእግዚአብሔር እንደ መጠሪያ ጥቅም ላይ የዋለ ቃል ሲሆን በዚህ ቦታ ላይ መጠቀሱ እግዚአብሔር እየተባለ ያለው የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን ያረጋግጣል። ምክንያቱም በዘፍ 31:10-13 ላይ የእግዚአብሔር መልአክ "..የቤቴል አምላክ እኔ ነኝ.." ሲል የተጠቀመው ቃል ይህን ቃል ነው።
"11 #የእግዚአብሔርም_መልአክ በሕልም። ያዕቆብ ሆይአለኝ፤ እኔም። እነሆኝ አልሁት 12 እንዲህም አለኝ። ዓይንህን አቅንተህ እይ፤ በበጎችና በፍየሎች ላይ የሚንጠላጠሉት የበጎችና የፍየሎች አውራዎች ሽመልመሌ መሳዮችና ዝንጕርጕሮች ነቁጣ ያለባቸውም ናቸው፤ ላባ በአንተ ላይ የሚያደርገውን ሁሉ አይቼአለሁና 13 ሐውልት የቀባህበት በዚያም ለእኔ ስእለት የተሳልህበት #የቤቴል_አምላክ_እኔ_ነኝ፤ አሁንም ተነሥተህ ከዚህ አገር ውጣ፥ ወደ ተወለድህበትም ምድር ተመለስ" (ዘፍ 31:11-13)
"የቤቴል አምላክ እኔ ነኝ" በሚለው ሀረግ "አምላክ" ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ዘፍ 35:1 ላይ ያለው ራሱ "אֵל֙/ኤል" የሚለው ቃል ነው (Strong's H410) ዘፍ 31:11-13 ላይ ግን ሲጠቀስ ከውስን መስጻምር ወይም definite article ጋር ነው። ስለዚህ "הָאֵל/ሀ ኤል" ወይም "The God" ማለት ነው። በኢንግሊዘኛው ትርጉም ላይም "The God of Bethel" ተብሎ ተተርጉሟል። በዘፍ 35:1 እና በዘፍ 31:10-13 መካከል ካለው አውዳዊ/contextual አንድነት ባሻገር ይህን አይነት ሰዋሰዋዊ/grammatical አንድነት መኖሩ ያዕቆብ መሠዋት የሰራለት እግዚአብሔር የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን ያረጋግጣል።
✍️ በዘፍ 35:1 ላይ እግዚአብሔር በሶስተኛ መደብ የተናገረውም ለዚህ ነው። እግዚአብሔር አምላክ በዘፍ 35:1 ላይ ያዕቆብን መሠዊያ እንዲሰራ ሲያዝዘው "ለእኔ ስራልኝ" አላለውም። በሶስተኛ መደብ "ለተገለጠልህ እግዚአብሔር መሠዊያ ስራ" ነበር ያለው። በሶስተኛ መደብ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ስራ ያለው እግዚአብሔር ብሎ እየጠራ ያለው ልጁ/መልአኩ ስለነበር ነው። እግዚአብሔር አምላክ ለልጁ ለኢየሱስ ክርስቶስ አምልኮ እንዲቀርብ ያዘዘበት የብሉይ ኪዳን ክፍል ነው።
ባለፉት ተከታታይ ክፍሎች ለማየት እንደሞከርነው ጌዴዎን ከእርሱ በፊት የተጻፉትን ቅዱሳት መጻሕፍት የሚያውቅ ሰው ነው (መሳ 6:13) ምክንያቱም በኦሪት ላይ እስራኤላውያን የኦሪትን ቃል በሙሉ በዕለት ተዕለት ኑሯቸው እንዲጫወቱት፥ እንዲያሰላስሉት በእግዚአብሔር ቃል ታዝዘዋልና (ዘዳ 6:6-9) ጌዴዎንም ይህንኑ ያደርግ ስለነበር ከእርሱ ዘመን በፊት የተጻፈውን ኦሪት ያውቃል። ስለዚህ አሁን ባየነው የኦሪት ክፍል ላይ የእግዚአብሔር መልአክ መሥዋዕት እንደቀረበ ያውቅ ነበር። ይህ ማለት ለእግዚአብሔር መልአክ መሥዋዕት ማቅረብ እንደሚቻል ያውቃል ማለት ነው። ስለዚህ ይህን ስለሚያውቅ የእግዚአብሔር መልአክ ሲገለጥለት እርሱ መሆኑን ለማረጋገጥ መሥዋዕት አቀረበለት። ይህ የእግዚአብሔር መልአክ መለኮት መሆኑን በሚገባ ያረጋግጣል።
ወደ ያዕቆብ ታሪክ ስንመለስ፥ ያዕቆብ ወደ ቤቴል ሄዶ መሠዊያ እንዲሰራ ከታዘዘ በኋላ ቤተሰቡንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሁሉ እንግዶችን አማልክት ከመካከላቸው እንዲያስወግዱ፥ ንጹሐንም እንዲሆኑ፥ ልብሳቸውንም እንዲለውጡ ይነግራቸዋል (ዘፍ 35:2) ከዚያም በመከራው ጊዜ ለሰማው በሄደበት መንገድ ከእርሱ ጋር ለነበረው እግዚአብሔር መሠውያንን እንደሚያደርግ ይገልጽላቸዋል። የመከራዬ ጊዜ የሚለው በዘፍ 32 ላይ ወንድሙ ዔሳው ወደ እርሱ የመጣበትን ክስተት ሲሆን፥ በዚያ ጊዜ ጸሎቱ ሰምቶ ያዳነው አምላክ የእግዚአብሔር መልአክ ነው (ዘፍ 32:9-12 ዘፍ 32:24-30) እንዲሁም በሄደበት ሁሉ ከእርሱ እንደሚሆን ቃል የገባለት የእግዚአብሔር መልአክ ነው (ዘፍ 28:15/ዘፍ 31:11-13) ይህ በዘፍ 35:1 ላይ ከተሰጠው ትዕዛዝ ባሻገር በእርግጥም መሠዊያ እየሰራ የነበረው ለእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን ያረጋግጣል።
▶️ ይቀጥላል