የኦሮሚያ ንግድ ምክር ቤት ከጆርካ ኢቨንትስ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ዓለም አቀፍ የቡና አውደ ርዕይ በጅማ ከተማ በይፋ ተከፍቷል።
የመክፈቻ ስነ-ስርዓቱን የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎች፣ ሃደ ስንቄዎች እና የሃይማኖት አባቶች በምርቃት የከፈቱት ሲሆን ለታዳሚዎቹም የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የዳሸን ባንክ ቺፍ ስትራቴጂ ኦፊሰር አቶ አየለ ተሾመ፣ ባንኩ ለቡና ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ ያለውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ባንኩ በጅማና አካባቢው ለሚንቀሳቀሱ ላኪዎችና (Exporters) ባለድርሻ አካላት የፋይናንስ አቅርቦት በማመቻቸት ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ይህንንም ድጋፍ አጠናክሮ በማስቀጠል የሀገሪቱን የቡና ኤክስፖርት ገቢ ለማሳደግ ሀገራዊ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።
የኦሮሚያ ክልል የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ተወካይ አቶ ነጂብ ከድር በበኩላቸው፣ ቡና የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት ከመሆኑም ባለፈ ማህበራዊ ትስስርን የሚያጠናክርና ከማሳ እስከ ዓለም አቀፍ ገበያ ድረስ ለበርካቶች የስራ ዕድል የፈጠረ ዘርፍ መሆኑን አስረድተዋል።
በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለቡና ጥራት ከመሰረቱ በጋራ መስራት እንዳለባቸው ያሳሰቡት አቶ ነጂብ፣ ዳሸን ባንክ ለዘርፉ እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።