ሥውር ትስስሮችን በማጋለጥ፣ በስፖርት ዘርፍ ከሙስና ወለድ ወንጀሎች እንታደግ!
**
በሥውር ትስስሮች አማካኝነት ከሚፈጸሙ የሙስና ወለድ ወንጀሎች መካከል በስፖርት ዘርፍ የሚስተዋሉት የሙስና ድርጊቶች ተጠቃሽ ናቸው። ስፖርት የችሎታ፣ የፍትሐዊነት፣ የዲሲፕሊንና የታማኝነት መገለጫ ቢሆንም፣ በዘርፉ የሚፈጸሙ የሙስና ወንጀሎች የውድድርን ፍትሐዊነት ከማዛባት ባለፈ የሀገርን ሀብት፣ የስፖርቱን እድገትና የሕዝብን እምነት ይጎዳሉ።
እነዚህ ወንጀሎች በሕገወጥ ስምምነትና በመመሳጠር ስለሚፈጸሙ፣ ከምንጫቸው ለመከላከል ከጀርባቸው ያሉትን ሥውር ትስስሮች መለየት፣ ማጋለጥና መበጣጠስ ያስፈልጋል።
በስፖርት ዘርፍ ከሚፈጸሙ የሙስና ድርጊቶች መካከል በጉቦና በሥውር ስምምነት የአትሌቶችንና የተጫዋቾችን ምርጫና ምደባ ማዛባት፣ የዳኞችን ውሳኔ በሕገወጥ መንገድ ማሳለፍ፣ የውድድር ውጤትን ለመቀየር መመሳጠር እንዲሁም የአትሌቶችንና የተጫዋቾችን ዕድሜ ወይም ብቃት ሐሰተኛ ሰነዶችን መጠቀም ይገኙበታል።
በተለይም በእግር ኳስ ዘርፍ የተጫዋቾች ዝውውርና የውል ሂደቶች ለሙስና ተጋላጭ ናቸው። የዝውውር ዋጋን ከእውነተኛው በታች ማሳየት፣ የውል ክፍያዎችን ማጋነን ወይም መደበቅ፣ ያልተገባ ኮሚሽንና ጉቦ መቀበል፣ ውሎችን በሥውር ስምምነት ማደራጀትና የዝውውር ገንዘብን ለግል ጥቅም ማዋል የዚህ ዓይነት ድርጊቶች ናቸው። በእነዚህ ሂደቶች የክለብ አመራሮች፣ የተጫዋቾች ወኪሎች፣ ደላሎችና ሌሎች ተዋናዮች በመመሳጠር ሕገወጥ ጥቅም ሊያገኙ ይችላሉ።
ከዚህ በተጨማሪ ለስፖርት የተመደበ በጀትና ቁሳቁስ ለግል ጥቅም ማዋል፣ በግዥና በስፖርት ተቋማት ግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ ማጭበርበር፣ የክለቦችንና የፌዴሬሽኖችን ገቢ አላግባብ መጠቀምም በዘርፉ የሚስተዋሉ የሙስና ድርጊቶች ናቸው።
በእነዚህ ወንጀሎች የሚሳተፉ አካላትም ሕገወጥ ጥቅማቸውንና የወንጀል ፍሬያቸውን ለመደበቅ ሐሰተኛ ሰነዶችን ማዘጋጀትና የተደራረቡ የገንዘብ ዝውውሮችን መፈጸም የመሳሰሉ ሕገወጥ ዘዴዎችን ሊጠቀሙ ይችላሉ።
እነዚህ ድርጊቶች ብቁ አትሌቶችና ተጫዋቾች በችሎታቸው ፈንታ በዝምድና በጉቦ እንዲመረጡ ወይም እንዲገለሉ፣ የስፖርት ሀብት ለታለመለት ዓላማ እንዳይውልና የክለቦችና የፌዴሬሽኖች ተዓማኒነት እንዲቀንስ ያደርጋሉ። ከዚህም በላይ የወጣቶችን ተስፋ በማጨለም፣ በችሎታና በትጋት ስኬት ማምጣት እንደሚቻል ያላቸውን እምነት ያዳክማሉ።
ይህንን ለመከላከል የስፖርት ተቋማት፣ ክለቦችና ፌዴሬሽኖች ግልጽነትንና ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥ አሠራር መዘርጋት፣ የአትሌቶችንና የተጫዋቾችን ምርጫና ምደባ በግልጽ መስፈርት መፈጸም፣ የዝውውርና የውል ሂደቶችን በሕጋዊና በተመዘገበ መንገድ ማከናወን፣ የገንዘብ ፍሰትን መቆጣጠርና አጠራጣሪ ድርጊቶችን በአግባቡ መመርመር ይጠበቅባቸዋል።
በተመሳሳይ፣ አትሌቶች፣ ተጫዋቾች፣ አሰልጣኞች፣ ዳኞችና የተጫዋቾች ወኪሎች ሙያዊ ሥነምግባርን በመጠበቅና ከሕገወጥ ስምምነቶች በመራቅ የስፖርቱን ንጹሕነት እና ከብልሹ አሠራር ነፃ መሆን ለማረጋገጥ የድርሻቸውን መወጣት አለባቸው።
ሕብረተሰቡም በስፖርት ውስጥ በሚከናወኑ የአትሌቶችና የተጫዋቾች ምርጫ፣ በዝውውርና በውል ሂደቶች፣ በውድድር ውጤትና በሀብት አጠቃቀም ዙሪያ አጠራጣሪ ድርጊቶችን ሲያስተውል፣ በተጨባጭ መረጃና ማስረጃ በመደገፍ ለሚመለከተው አካል ጥቆማ መስጠት ይኖርበታል።
የስፖርት ዘርፉን ከሙስና ወለድ ወንጀሎች ለመታደግ የሚታዩ ሕገወጥ ድርጊቶችን ብቻ መቃወም በቂ አይደለም፤ ከጀርባቸው ያሉትን ሥውር ትስስሮች መፈለግ፣ ማጋለጥና መበጣጠስ ያስፈልጋል። ስለሆነም የስፖርት ተቋማት ተጠያቂነትን ሲያረጋግጡ፣ ሕብረተሰቡም በመረጃና በማስረጃ ሙስናን በማጋለጥ የድርሻውን መወጣት ይገባል።
ሥውር ትስስሮችን በማጋለጥ፣ የሙስና ወለድ ወንጀሎችን ሰንሰለት እንበጥስ!
የሙስና ወንጀል መጠቆሚያ አማራጮችን፣ ወቅታዊ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት👇🏾
#NCRS ሞባይል መተግበሪያ
#ለAndroid ስልክ ተጠቃሚ ጠቋሚዎች
https://play.google.com/store/apps/details...
#ለApple or iPhone ስልክ ተጠቃሚ ጠቋሚዎች
https://apps.apple.com/us/app/ncrs/id659366231በስልክ ቁጥር ለመጠቆም፦ 0953222299/55
ለሀብት ማሳወቅና ምዝገባ፦
https://feaccears.gov.et/ዌብሳይት፦
https://www.feacc.gov.etፌስቡክ፡-
https://www.facebook.com/feaccOfficial/ቴሌግራም፦
https://t.me/feaccዩትዩብ፡-
https://www.youtube.com/@federalethicsanti-corrupti149ትዊተር፦
https://twitter.com/EthiopiaFeacc በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡