----------------
የቀድሞ የምክር ቤት አባል የነበሩት አቶ ዮሐንስ ካሳሁን ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
አቶ ዮሐንስ ካሳሁን በ5ኛው የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሸካ ዞን ቴፒ ምርጫ ክልልን ህዝብን ወክለው አገልግለዋል።
አቶ ዮሐንስ ካሳሁን ከአባታቸው ከአቶ ካሳሁን ማሞ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ማርታ ቶጋ በ1974 ዓ.ም በሸካ ዞን የኪ ወረዳ፣ ሻይ ቀበሌ፣ ኩራች መንደር ተወለዱ።
አቶ ዮሐንስ ከ1ኛ እስከ 7ኛ ክፍል ትምህርታቸውን በቴፒ ሙሉ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረዋል። በመቀጠልም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአርባ ምንጭ አዳሪ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።
አቶ ዮሐንስ ካሳሁን ለትምህርትና ለሙያ እድገት የነበራቸውን ቁርጠኝነት በማሳየት በመምህርነት ዲፕሎማ እንዲሁም በማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል።
በሙያዊና በአመራር ሕይወታቸውም በመምህርነት በማገልገል ጀምረው፣ በዞኑ መዋቅር በመምሪያ ኃላፊነት ድረስ አገልግለዋል።
አቶ ዮሐንስ በ5ኛ ዙር ሀገር አቀፍ ምርጫ በሸካ ዞን ቴፒ ምርጫ ክልልን ወክለው ለፓርላማ በመወዳደር የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል በመሆን ህዝባቸውን አገልግለዋል።
በመጨረሻም የዞኑ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ በመሆን ለሕዝባቸውና ለዞኑ እድገት ለበርካታ ዓመታት በኃላፊነት ሲያገለግሉም ነበር።
አቶ ዮሐንስ በ1996 ዓ.ም ትዳር የመሠረቱ ሲሆን ፤ በትዳራቸውም ሁለት ወንድና ሁለት ሴት በድምሩ አራት ልጆችን አፍርተው ነበር።
አቶ ዮሐንስ ካሳሁን ህዳር 4 ቀን 2019 ዓ.ም በ45 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሲሆን፤ የቀብር ስነ-ስርዓታቸውም በሸካ ዞን የኪ ወረዳ በአዲስ ብርሃን ቀበሌ ወዳጅ ዘመዶቻቸውና ወዳጆቻቸው በተገኙበት ተፈፅሟል።
የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም በአቶ ዮሐንስ ካሳሁን ህልፈት የተሰማውን ሀዘን እየገለጸ፤ ለሟች ቤተሰቦች፣ ለወዳጅ ዘመዶች በሙሉ መፅናናትን ይመኛል።