Телеграм

ፍልስፍና ለላቀ አስተሳሰብ

@Zephilosophy История и философия
РКН: проверяем Не иноагент
✨Philosophy For Higher Consciousness✨

Статистика обновлена 14.11.2026 в 23:44 · 1 просмотр страницы · Хотите больше просмотров?

Подписчики32 824
Охват поста9 466 29% от подписчиков
ERR за месяц28,84%
ERR за 24 часа8,14%

Динамика за 30 дней

Рекламные публикации

Рекламных публикаций не найденоЗа последнее время мы не нашли на площадке ни одного рекламного поста.

Последние публикации

Все посты канала →
ፍልስፍና ለላቀ አስተሳሰብ tg32 тыс. подписчиков
Открыть пост ↗
የምክንያታዊ ነፍስ ተፈጥሮ
Marcus Aurelius
📖Meditation

ሂፖክራተስ ብዙ በሽተኞችን አከመ፤ በኋላ ግን ራሱ ታሞ ሞተ። ኮከብ ቆጣሪዎች የብዙ ሰዎችን ሞት ተነበዩ፤ በመጨረሻ ግን የራሳቸውም ሰዓት ደረሰ። ብዙ ከተሞችን ያጠፉና በጦርነት በሺህ የሚቆጠሩ ወታደሮችን የገደሉት እነ ታላቁ እስክንድር፣ ፖምፔ እና ቄሳርም ከዚህ አለም ተሰናበቱ። አለም በእሳት ትጠፋለች እያለ ሲሰብክ የነበረው ሄራክሊተስ ሰውነቱ ውሃ ቋጥሮ በጠና ታሞ ሞተ። ዴሞክሪተስን ተራ ተባዮች ገደሉት፤ ሶቅራጥስን ደግሞ ሰው የተባሉ ተባዮች ገደሉት። ይህ ምን ማለት ነው? መርከብ ላይ ተሳፍረሃል፣ ጉዞህን ጨርሰህ የምትወርድበት ሰዓት ይደርሳል።

በየቀኑ የሕይወታችን ክፍል እየተሸረሸረና የቀረው ጊዜ እያጠረ መምጣቱ ብቻ ሊያሳስበን አይገባም፡፡ ይህንንም ማሰብ አለብን፦ ዕድሜያችን ቢረዝም እንኳ፤ ዓለምን ለመረዳትና መለኮታዊ እንዲሁም ሰብአዊ እውቀቶችን ለመመርመር የሚያስችል የአእምሮ ብቃት እንደቀድሞው አብሮን እንደሚዘልቅ እርግጠኛ መሆንስ እንችላለን? ምክንያቱም አእምሯችን መጃጀት ከጀመረ መተንፈስ፣ መብላት፣ ማሰብና ስሜታዊ መሆን አናቆም ይሆናል። ነገር ግን እምቅ አቅማችንን መጠቀም፣ ግዴታችንን መለየት፣ የምንሰማውንና የምናየውን መተንተን እነዚህ ሁሉ ነገሮች ጤናማ አእምሮ የሚጠይቁ ናቸውና ይጠፋሉ። ስለዚህ መፍጠን አለብን፡፡ ወደ ሞት በየቀኑ እየቀረብን ከመሄዳችንም ባሻገር ነገሮችን የመረዳትና
የአለምን ሁኔታ የመገንዘብ አቅማችን ሕይወታችን ከማለፉ በፊት ሊጠፋም ይችላል።

በግዳጅ ሳይሆን በፈቃደኝነት፣ በራስ ወዳድነት ሳይሆን ለጋራ ጥቅም፣ ያለ ጥንቃቄ ሳይሆን በምክንያት፣ በፍርሃት ሳይሆን በልበ ሙሉነት ሥራ። ሃሳብህን አትቀባባ፡፡ አላስፈላጊ ቃላትን አትናገር፤ ብዙ ነገሮች ውስጥ አትግባ። በውስጥህ ያለው መንፈስ የወንድን፣ የብስለትን፣ የመሪን ስብዕና ይላበስ፡፡ ቦታውን እንደያዘና የመጠራትን ጥሪ በትዕግስት እንደሚጠብቅ፣ መሐላ ወይም ምስክር እንደማያስፈልገው ወታደር ሁን። በራስህ ደስተኛ ሁን፤ የሌሎችን እርዳታ ወይም ከሌሎች የሚገኝ ሰላምን አትጠበቅ᎓᎓ በራስህ ቀጥ በል እንጂ በሌሎች ድጋፍ አትቁም፡፡

የጠራና የተስተካከለ ሰው አእምሮ ውስጥ ቆሻሻ የለም፡፡ ሕይወቱ በሞት ሲቋረጥ፣ ተውኔቱ ሳያልቅ እንደሚያቋርጥ ተዋናይ አይሰማውም᎓᎓ ባርነት ወይም ትዕቢት አይታይበትም᎓᎓ ማጎብደድ ወይም ንቀት የለበትም። ሰበብ መደርደር ወይም መሸሽ የለበትም፡፡

አስተሳሰብህን የመቆጣጠር ችሎታህን አክብረው:: አእምሮህ ለተፈጥሮህና ለምክንያታዊ ፍጥረታት የማይስማማ የተሳሳተ አመለካከት እንዳይኖረው የሚጠብቅህ እርሱ ብቻ ነው። ማስተዋልን፣ ለሰዎች ፍቅርን እና ለመለኮታዊ ፈቃድ መገዛትን የሚያስችልህም ይህ ችሎታ ነው፡፡

ፈጽሞ አስታውስም፦ እያንዳንዳችን የምንኖረው አሁን በዚህች ቅጽበት ብቻ ነው:: የቀረው ጊዜ ወይ አልፏል፣ ወይም ገና ስላልመጣ አይታወቅም፡፡ የምንኖርበት ጊዜ አጭር ነው፤ የምንኖርባትም ምድር ጠባብ ናት:: ትልቁ ዝናም ቢሆን አጭር ነው፡፡ ስለራሳቸውም ሆነ ቀድሞ ስለሞቱት ምንም በማያውቁ ሰዎች በአንደበታቸው ሲላላኩት የሚጠፋ ነው፡

ትናንት የዘር ጠብታ ፤ ነገ አመድ ነህ። ይህችን አጭር ጊዜ ተፈጥሮ በሚጠይቀው መንገድ አሳልፈው:: የወለደችውን ምድር እያመሰገነ፣ ያሳደገውን ዛፍ እያከበረ፤ በለስ ሲበስል እንደሚወድቅ፣ ያለ ጩኸትና ቅሬታ ሕይወትን ተሰናበታት፡፡

ማዕበል በላዩ ላይ እንደሚገለባበጥበት ጽኑ ዓለት ሁን፡፡ እርሱ ሳይናወጥ ይቆማል፤ የባሕሩም ቁጣ በዙሪያው ፀጥ ይላል፡፡

“ይህ ነገር በኔ ላይ የደረሰው እድለቢስ ስለሆንኩ ነው” ትላለህ? እንዲህስ አይደለም፡፡ ይልቁንስ “ይህ ቢደርስብኝም እንኳ፣ በአሁኑ ሳልሰበር፣ ስለሚመጣውም ሳልጨነቅና ሳልፈራ፣ ያለ ሐዘን በጽናት ስለምወጣው የታደልሁ ነኝ” ልትል ይገባሃል።"

ይቀጥላል..
@zephilosophy
👁 2.7 тыс. 👍 33❤ 26🔥 8 💬 3 ↻ 19 12 ноября
ፍልስፍና ለላቀ አስተሳሰብ tg32 тыс. подписчиков
Открыть пост ↗
የኃይል ፈቃድ (Will to Power)
​«ሕያው ፍጥረት ከሁሉም በላይ ኃይሉን መልቀቅ ይሻል፤ ሕይወት ራሷ የኃይል ፈቃድ ናት።» — ኒቼ

​አንዲት ሕፃን መራመድ ስትለማመድ ትወድቃለች፣ ትነሳለች፣ እንደገናም ትሞክራለች። በሕይወት ለመቆየት መራመድ አያስፈልጋትም፤ መዳህ ወይም መቀመጥ ትችላለች። ታዲያ ቀደሞውኑ ማድረግ በምትችለው ነገር ሳትረካ እንዲህ እንድትተጋ የሚያደርጋት ምንድን ነው?

የነርቭ ሳይንቲስት ሂደቱን ማብራራት ይችላል። የፊዚዮሎጂ ባለሙያ ጡንቻዎችን፣ ሚዛንን እና እየዳበረ የሚሄደውን የእንቅስቃሴ ቅንጅት መግለጽ ይችላል። የስነ-ልቦና ባለሙያ ደግሞ ስለ መማር፣ መኮረጅ (imitation) እና ማጠናከሪያ ማስረዳት ይችላል። እነዚህ ሁሉ ማብራሪያዎች ሙሉ በሙሉ ትክክል ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን ፍልስፍና ሁልጊዜም ማብራሪያው ምክንያታዊ መስሎ መታየት ከጀመረ በኋላ እንኳን ጥያቄዎችን መጠየቅ የመቀጠል አስገራሚ ባህሪ አለው።

ባለበት ለመቆየት አሻፈረን የሚለው ይሄ በውስጣችን ያለው እንቅስቃሴ ምንድን ነው?

ለምንስ ነው አብዛኛውን ጊዜ ራሳችንን ከመጠበቅ (preserve ከማድረግ) ባለፈ፣ ትናንት ከነበርነው የበለጠ አቅም ያላቸው ለመሆን የምንፈልገው?

ግልጹ መልስ ህልውናን ማስቀጠል (survival) ነው። ሕያው ፍጥረታት ህልውናቸውን ማስቀጠል አለባቸው። ምግብ፣ መጠለያ፣ መራባት እና ከአደጋ መከለል ያስፈልጋቸዋል። አብዛኛው የባህሪ ዓይነት በሕይወት ከመቆየት ግፊት አንጻር ልንረዳው ይችላል።

ሌላው መልስ ደግሞ ደስታ (pleasure) ነው። ምናልባት ጥሩ ስሜት ያለውን እንፈልጋለን፤ የሚያመንን ደግሞ እንሸሻለን።

በሁለቱም ማብራሪያዎች ውስጥ እውነት አለ። ግን የሰው ልጅ ሕይወት እነዚህን ማብራሪያዎች ተሻግረው የሚፈሱ ምሳሌዎችን እንዳሳየን ነው።

ቀድሞውኑ በቂ ገንዘብ ያለው ሰው የበለጠ ይፈልጋል። አንድ ሰዓሊ ሀብታም ሊያደርገው የማይችል ነገር ለመፍጠር አስር ዓመታት ያሳልፋል። አንድ የሂሳብ ሊቅ ምንም ዓይነት ቀጥተኛ ተግባራዊ ጥቅም የሌለውን ችግር ለመፍታት ሌሊቶችን ቁጭ ብሎ ያድራል። አንድ ደራሲ ሰዓታትን ወስዶ የጻፈውን ገጽ ገና እንደፈለገ ስላልሆነለት ይቀደዋል። የሆነ ሰው በጫፉ ላይ የሚጠብቀው ምንም ዓይነት ሀብት የሌለበትን ተራራ ይወጣል። ሌላው መናገር መቻል ስለፈለገ ብቻ ከባድ ቋንቋ ይማራል። አንድ ሰው የማይመግበውን፣ የማያስከፍለውን ወይም ሕይወቱን የማያድንለትን ሀሳብ ለመረዳት ዓመታትን ያሳልፋል።

እና ደግሞ ሆን ብለው ፈታኝ ነገሮችን የሚመርጡ ሰዎችም አሉ።

ምቾትን የሚተው መነኩሴ፤ ከአስደሳች ቅዠት ይልቅ የሚረብሽ እውነትን የሚመርጥ ፈላስፋ፤ ሰውነቱን ከቀደመው ወሰን በላይ የሚገፋ ስፖርተኛ፤ ቀላል ስታይሎችን የማይቀበል አርቲስት፤ መላመድን መሸከም አቅቶት የተለመደ ሕይወቱን ትቶ የሚሄድ ሰው።

ለመሆኑ እነዚህ ሰዎች ምን እየፈለጉ ነው?

ምናልባት ኒቼ በምኞታችን ግብ ላይ ብቻ ከመጠን በላይ እንዳተኮርንና ከጀርባው ስላለው ኃይል ግን በቂ ትኩረት እንዳልሰጠን ይነግረን ይሆናል።

እኛ አንድ ሰው ምን እንደሚፈልግ እንጠይቃለን።

ኒቼ ግን በዚያ ሰው ውስጥ የሚያልፈውና የሚያንቀሳቅሰው ነገር ምን እንደሆነ ይጠይቃል።

ከዚያም ከታዋቂ ጽንሰ-ሃሳቦቹ አንዱ ይመጣል: «የኃይል ፈቃድ (Will to power)»።

አብዛኛውን ጊዜ ፍላጎትን ወይም ፈቃድን እንደ ንቁ አእምሯዊ ውሳኔ እናስበዋለን። እወስናለሁ። እመርጣለሁ። እፈልጋለሁ። እሰራለሁ። እንላለን

ኒቼ ግን ጭንቅላታችን ውስጥ ተቀምጦ ለሁሉም ነገር ትእዛዝ የሚሰጠውን ይህን ትንሽ ገዢ በጥርጣሬ ነው የሚያየው። በኒቼ የስነ-ልቦና እይታ፣ የሰው ልጅ እንደሚታየው አንድ ወጥ (unified) አይደለም። በተለያዩ አቅጣጫዎች የሚንቀሳቀሱ ስሜታዊ ግፊቶች፣ ልምዶች፣ ምኞቶች፣ ፍርሃቶች፣ ተፈጥሯዊ ድራይቮች እና የተወረሱ እሴቶች አሉ። “እኔነት/the self” የምንለው ነገር መንግስቱን እንደሚገዛ ንጉሥ ሳይሆን፣ እርስ በርስ በሚፎካከሩ ኃይሎች መካከል ያለ ጊዜያዊ ስምምነት ወይም arrangement ሊሆን ይችላል።

አንዳንዴ “ማድረግ ስለፈለግኩ ነው ያደረግኩት” እንላለን፤ ነገር ግን እውነተኛ ትርጉሙ በውስጣችን ያለው አንድ ነገር በውስጣችን ካሉት ሌሎቹ ነገሮች ላይ የበላይነት አገኘ ማለት ነው

ምቾትን እንፈልጋለን፤ ግን ስኬትንም እንፈልጋለን።
እውነትን እንፈልጋለን፤ ግን ከቅዠቶቻችን የምናገኘውን መጽናኛም እንፈልጋለን።
መደነቅ እንፈልጋለን፤ ግን አንዳንዴ ሙሉ በሙሉ ለብቻችን መተው እንፈልጋለን።

የሰው ልጅ በነዚህ መሰል ተቃርኖዎች የተሞላ ነው።

ስለዚህ በኒቼ ዘንድ “ፈቃድ” ወይም “ፍላጎት” እንደ ተራ ንቁ ምኞት ብቻ መወሰድ የለበትም፣ ምክንያቱም ሃሳቡ ከንቁ ምኞት ይልቅ ወደ ጥረት፣ ወደ ውስጣዊ ግፊት እና ወደ ኃይሎች እንቅስቃሴ የቀረበ ነው።

ኃይል" የሚለውን ቃልም ስንረዳ በቀላሉ የበላይነትን (domination) ብቻ መምሰል የለበትም፦
​ኃይል ማለት የመንቀሳቀስ፣ የመቋቋም፣ የመለወጥ እና ለአንድ ነገር ቅርጽ የመስጠት አቅም ነው።

ራስን ማሸነፍ (self-overcoming) ማለት ማልዶ መንቃት፣ ጂም መሄድ፣ ገንዘብ መስራት እና የበለጠ ውጤታማ መሆን ብቻ አይደለም። የኒቼ ጥያቄ በጣም የበለጠ ረባሽ ነው።

ልታሻሽለው የምትሞክረው ሰው የተገነባው በፍጹም መርጠሃቸው ከማታውቃቸው እሴቶች ቢሆንስ?

ብርቱ መሻትህ የተወረሰ ቢሆንስ?

ስለ ስኬት ያለህ ሀሳብ ከአንተ ይልቅ የማህበረሰብህ ቢሆንስ?

ልዩ የመሆን ፍላጎትህ በራሱ ሌላ የታዛዥነት ዓይነት ብቻ ቢሆንስ?

ኒቼ ዛሬም ረባሽ የሆነው እሴቶች ከሰማይ እንዳልወረዱ ስለሚያሳይ ነው። ከየት መጡ? ምን ዓይነት ሰው እንደፈለጋቸው? ምን ዓይነት ሕይወትን እንዳገለገሉ? በእነሱ በኩል ምን ዓይነት ኃይሎች እንደተገለጹ ይጠይቃል።

ዋጋ ያለው ምንድን ነው?
ምን ክቡር፣ ምን ኃጢአት፣ ምን ጠንካራ፣ ምን ደካማ እንደሚባል ይጠይቃል? እናም ወደ ራሳችን ይመልሰናል፦ የምትፈልጉትን እንድትፈልጉት ያስተማራችሁ ማነው? ማንም ባያያችሁ ከብርቱ መሻታችሁ ምን ይቀራል? ማንም ባያመሰግናችሁ ከሞራላችሁ ምን ይተርፋል?

ግን እዚህ ላይ ኒቼን መቃወም አለብን ብዬ አስባለሁ። የሰው ልጅ ወደ አንድ ዋና ግፊት/ድራይቭ አይቀነስም። ደህንነትንና ነፃነትን፣ እውነትንና ምቾትን፣ እውቅናንና ብቸኝነትን እንፈልጋለን፤ ራሳችንን መጠበቅ እንፈልጋለን፣ አንዳንዴም ከራሳችን ማለፍ። ስለዚህ የኃይል ፈቃድ እንደተረጋገጠ ሳይንሳዊ ሕግ ወይም እያንዳንዱን እንቆቅልሽ የሚከፍት ምትሃታዊ ቁልፍ ሳይሆን ጥያቄ፣ መነፅር እና መቀስቀሻ ቢሆን ይሻላል። ሲጠቀሙበት አንድ ነገር ይታያል፤ ዞር ሲያደርጉት ሌላ ነገር ይመለሳል።

አንዲት ሕፃን በክፍሉ መሃል ትቆማለች። ትወድቃለች። ትነሳለች። እንደገና ትሞክራለች። ምናልባት መራመድ እየተማረች ነው። ምናልባት የኃይል ፈቃዷን እየገለፀች ነው። ምናልባትም ሕያው ነች። እነዚህ ሦስቱ መጀመሪያ እንደሚታዩት የተራራቁ ላይሆኑ ይችላሉ፣ ምክንያቱም ከታላላቅ ቃላት በታች ትንሽ የሚያስደንቅ እውነት አለ፦ እኛ አላለቅንም። ሁሌም የሆነ ነገር እየሆንን ነው።
ከባዱ ጥያቄ ኃይል አለን ወይ የሚለው አይደለም። ኃይላችን እኛን ምን እያደረገን ነው የሚለው ነው።
እናም ወድቆ እንደገና ለተነሳ ሰው ሁሉ የሚጠብቀው ጥያቄ ይህ ነው፦ ባለበት ቦታ ላይ ለመቆየት አሻፈረኝ የሚለው በውስጣችን ያለው ይህ ነገር ምንድን ነው?

ፀሀፊ- ዮናታን አቢስ

@zephilosophy
👁 6 тыс. ❤ 40👍 19🔥 5 💬 2 ↻ 25 6 ноября
ፍልስፍና ለላቀ አስተሳሰብ tg32 тыс. подписчиков
Открыть пост ↗
ኩርት ቮነጉት

የጦርነትን አሰቃቂነት እና የሰው ልጅ ዕብደትን በህይወቱ ተሞክሮ ልክ እንዳልሆነ አይቶ የሚያሳይ ደራሲ ነው፡፡ ኩርት ቮነጉት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በጀርመን ድሬስደን ከተማ የቦምብ ድብደባ ውስጥ ተይዞ ከሞት የተረፈ ሰው ነው። ይህ ገጠመኙ ጦርነት የጀግንነት ማሳያ ሳይሆን ንጹሐንን የሚጨፈጭፍ፣ ሰብአዊነትን የሚያጠፋ እና ትርጉም የለሽ አረመናዊ ድርጊት መሆኑን ይናገራል፡፡

ኩርት ቮነጉት በሞራል እና በፖለቲካ መካከል ስላለው  ግጭት "ማዘር ናይት" ብሎ በሰየመው ድረሰቱ  በጦርነት ጊዜ መንግሥታት ሕዝቦችን ለራሳቸው ዓላማ ሲሉ "ጥሩ" እና "ክፉ" ብለው ይከፋፍሏቸዋል ይለናል። ነገር ግን በግለሰብ ደረጃ "ለሀገር ብዬ ነው" "ተላላኪ ነበርኩ" ወይም "የትዕዛዝ ግዴታ ነው" ተብሎ የሚሰራው ክፉ ነገር የሰውን ህሊና እና እውነተኛ ማንነት ለዘላለም እንደሚበክለው ለማሳየት ይሞክራል።

ኩርት ቮነጉት "እኛ የምንመስለው የምንመስልበትን ነገር ነን" ይለናል፡፡ ይህም ማለት በውስጣችን ጥሩ ሐሳብ አለን ብንልም በውጭ ላይ የምንፈጽመው ተግባር ጥላቻን መስበክ፣ መከራን ማባባስ ይሆናል፡፡ ይህም በሂደት የእኛ እውነተኛ ማንነት ይሆናል ስለዚህ ድርጊታችን ከሐሳባችን ጋር ሊጣጣም ይገባል እያለ አበክሮ ይሞግተናል።

ኩርት ቮነጉት በጦርነትና በግጭት ጊዜ "እኛ ፍጹም ጻድቃን ነን፣ እነሱ ደግሞ ፍጹም ክፉዎች ናቸው" የሚለው አመለካከት የሐሰት ትርክት መሆኑን እና ሁለቱም ወገን የሰውን ልጅ ሕይወት እንደሚያጠፉ ያሳያል።

እንደ "ማዘር ናይት" ታሪክ ሁሉ ዛሬም በኢትዮጵያ ውስጥ በፖለቲካ እና በቡድን ስም ተነስተው ጥላቻን የሚሰብኩ ሕዝብን እርስ በእርስ የሚያጣሉ አካላት አሉ። ኋላ ላይ "ለዓላማ ብዬ ነው" ወይም "በትዕዛዝ ስር ስለነበርኩ ነው" "ተላላኪ ነበርኩ"  የሚሉ ማስተባበያዎች ቢቀርቡም በምድር ላይ የጠፋው ንጹህ ሕይወት እና የተበላሸው ማህበራዊ ትስስር ግን ሊመለስ አይችልም። ስለዚህ ማይክ በያዝን ወቅትም ሆነ አደበታችንን በከፈተን ጊዜ ሁሉ "ምን እየፈጠርን እና ምን እያስተላለፍን ነው?"ብሎ መጠየቅ የጊዜው ጥያቄ ነው።

በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ባሳለፈቻቸው ግጭቶችና ጦርነቶች ያየነው እውነት ቮነጉት ከድሬስደን ውድቀት ጋር ካስተማረው ትምህርት ጋር አንድ ነው። በጦርነት ውስጥ አሸናፊ የሚባል ወገን የለም፡፡ ሁለቱም ወገን የሚያጡት ወጣቶቻቸውን፣ ሰብአዊነታቸውን እና ሀገራዊ ሀብታቸውን ነው።

ስለሆነም ዛሬም ቆም ብለን ብናስብ፡፡ ለሕይወት እና ለአብሮነት መስጠት ያለብን ዋጋ ብንሰጥ በየቀኑ የሚሞተውን ህይወት መታደግ እንችላለን፡፡

ቮነጉት በድረስቱ እንዳለው  ሰው በምድር ላይ የሚቆየው እጅግ ለአጭር ጊዜ ነው። ይህችን አጭር ዕድሜ በጎጥ፣ በዘር እና በጥላቻ ከማጥፋት ይልቅ እርስ በእርስ በመተሳሰብ፤ ተፈጥሮን በመውደደ ና በመዋደድ የተሰጠንን የሕይወት ስጦታ በምስጋና ማሳለፍ እንዳለብን ይነግረናል፡፡

ቮነጉት በ"ካትስ ክሬድል" ስራው ላይ  እንዲህ እያለ ይቃትታል

"እግዚአብሔርም ብቸኛ ሆኖ ተሰማው። እግዚአብሔር ጭቃ ፈጠረ። ስለዚህ ለአንዳንድ ጭቃዎች እንዲህ አላቸው፦ "ተነስታችሁ ተቀመጡ!"

እግዚአብሔርም "የፈጠርኳቸውን ሁሉ ተመልከቱ፤ ኮረብታዎቹን፣ ባሕሩን፣ ሰማዩን፣ ከዋክብቱን" አለ።

እኔም ተነሥቼ እንድዞር እና እንድመለከት ከተደረጉት ጭቃዎች መካከል አንዱ ነበርኩ። ዕድለኛ ነኝ፡፡ ዕድለኛ ጭቃ!

እኔ ጭቃው ተነሥቼ ተቀመጥኩ፡፡ እግዚአብሔርም ምንኛ ድንቅ ሥራ እንደሠራ ተመለከትኩ። በጣም አሪፍ ሥራ ነው እግዚአብሔር!

ከአንተ በቀር ማንም ይህንን ሊያደርገው አይችልም ነበር፡፡ እግዚአብሔር ሆይ!
እኔማ ከቶውንም አልችለውም ነበር።

ከአንተ አንጻር ስታይ እኔ ከቶውንም ዋጋ የሌለኝ ሆኖ ይሰማኛል። እኔ ትንሽ መሆኔን ረሳሁ ብዬ የምፅናናበት ብቸኛ መንገድ ተነሥተው እንዲቀመጡ እና ዓለምን እንዲመለከቱ ዕድል ያልገጠማቸውን ያን ሁሉ ጭቃ ሳስብ ብቻ ነው።

እኔ ብዙ አገኘሁ፡፡ አብዛኛው ጭቃ ግን ይህ እድል አልሆነለትም። ለዚህ ታላቅ ክብርም አመሰግናለሁ!

አሁን ጭቃው እንደገና  ይተኛል። ጭቃው ሊኖሩት የሚችሉ ምን ያህል አስደናቂ ትዝታዎች ናቸው!

የገጠሙኝ ሌሎች አስደናቂ ተነስተው የተቀመጡ ጭቃዎች (ሰዎች) ምንኛ ድንቅ ነበሩ!

ያየሁትን ሁሉ ወደድኩት!" ይለናል፡፡

በየቀኑ የሰውን ልጅ የሞት ዜና መስማት ያማል ፡፡ በጋራ ለመዳን በጋራ መቆም አለብን፡፡ለየብቻው እና በየተራ የሚያለቅስ ህዝብ አይሻገርም!!

ፀሀፊ - ዮናስ ዘውዴ

@zephilosophy
👁 7.7 тыс. ❤ 53👍 5👏 3 💬 1 ↻ 14 2 ноября