ማረጥ የሴት የወር አበባ በቋሚነት የሚቆምበት የተፈጥሮ የሕይወት ደረጃ ነው። ይህ ለውጥ በአካላዊ ጤና ላይ ብቻ ሳይሆን በስሜት፣ በአስተሳሰብ፣ በባህሪና በግንኙነት ላይም ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል።
አንዳንድ ሴቶች በዚህ ወቅት ከዚህ በፊት የማያውቁትን የስሜትና የሥነልቦና ለውጦች ሊያጋጥማቸው ይችላሉ።
1. የስሜት መለዋወጥ (Mood Swings)
አንድ ቀን ደስተኛ ሆና ሌላ ቀን ያለ ግልጽ ምክንያት ሐዘንተኛ ልትሆን ትችላለች። በቀላሉ ልታዝን፣ ልትናደድ ወይም ልታለቅስ ትችላለች።
2. ጭንቀትና ያለመረጋጋት (Anxiety)
ከዚህ በፊት ብዙም የማያስጨንቋት ነገሮች ከመጠን በላይ ሊያስጨንቋት ይችላሉ። ያለ ምክንያት የመፍራት፣ የመረበሽና የልብ ምት መፍጠን ስሜት ሊኖራት ይችላል።
3. ቁጣና ብስጭት (Irritability)
በቀላሉ ልትበሳጭ፣ በትንሽ ነገር ልትናደድና ከቤተሰቦቿ ጋር በተደጋጋሚ ልትጋጭ ትችላለች። ይህም በትዳርና በቤተሰብ ግንኙነት ላይ ጫና ሊፈጥር ይችላል።
4. የእንቅልፍ መዛባት (Sleep Disturbance)
በሌሊት በተደጋጋሚ መንቃት፣ እንቅልፍ ማጣትና በቂ እረፍት አለማግኘት ሊያጋጥማት ይችላል። ይህም በቀጣዩ ቀን ድካም፣ ብስጭትና የትኩረት መቀነስ ያስከትላል።
5. የራስ መተማመን መቀነስ (Low Self-Esteem)
የሰውነቷ ቅርጽ፣ የቆዳዋ ለውጥ፣ የክብደት መጨመርና የወሲባዊ ፍላጎት መቀነስ በራሷ ላይ ያላትን እምነት ሊነኩ ይችላሉ። ራሷን ከዚህ በፊት እንደነበረችው ማየት ሊያቅታት ይችላል።
6. የማስታወስና የትኩረት ችግር (Brain Fog)
የተነገራትን ነገር መርሳት፣ ቃላትን ለማስታወስ መቸገር፣ በሥራ ላይ ትኩረት ማጣትና ውሳኔ ለመስጠት መቸገር ሊታይ ይችላል።
7. የድብርት ስሜት (Depressive Symptoms)
የማያቋርጥ ሐዘን፣ ከዚህ በፊት ደስ የሚያሰኛትን ነገር መጥላት፣ ተስፋ መቁረጥና ከሰዎች መራቅ ሊያጋጥማት ይችላል። አንዳንድ ሴቶች በዚህ ወቅት ለመጀመሪያ ጊዜ የድብርት ምልክቶች ሊያሳዩ ይችላሉ።
8. የወሲባዊ ፍላጎት መቀነስ
የሆርሞን ለውጥ፣ የእንቅልፍ መዛባት፣ የሴት ብልት ድርቀትና የስሜት ለውጥ የወሲባዊ ፍላጎቷን ሊቀንሱ ይችላሉ። ይህም በትዳር ውስጥ አለመግባባት ሊፈጥር ይችላል።
ባል ምን ማድረግ አለበት?
በዚህ ወቅት ባል ሚስቱን በቀላሉ መውቀስ፣ ስሜቷን ማቃለል ወይም ፍቅሯ ቀንሷል ብሎ መደምደም የለበትም።
1. ስሜቷን በትዕግሥት ያዳምጥ።
2. የሚያጋጥማትን ለውጥ እንድትናገር ደህንነት የሚሰማትን ሁኔታ ይፍጠር።
3. ከእሷ ጋር በማይጋጭ መንገድ የቤትና የቤተሰብ ኃላፊነትን ይጋራ።
4. ምልክቶቹ ከባድ ከሆኑ የሕክምና ድጋፍ እንድታገኝ ያበረታታት።
አስፈላጊ ማስታወሻ
እነዚህ ሁሉ ምልክቶች በሁሉም ሴቶች ላይ አይታዩም። ማረጥ ማለት የግድ ድብርት፣ የባህሪ መቀየር ወይም የግንኙነት መፍረስ ማለት አይደለም። የድብርትና የጭንቀት ምልክቶች ከቀጠሉ ወይም የዕለት ተዕለት ኑሮን ካስተጓጎሉ የጤና ባለሙያን ማማከር ያስፈልጋል።
ማረጥ የሴትነት መጨረሻ አይደለም። የሕይወት አዲስ ምዕራፍ ነው። በዚህ ምዕራፍ ሴትየዋ ከሁሉም በላይ የምትፈልገው መረዳት፣ ድጋፍና አክብሮት ነው።
ስለ ሥነልቦናና ግንኙነት ተጨማሪ ትምህርቶችን ለማግኘት ገጹን ተከታተሉ።
@binigirmachew