(አዲስ አበባ፤ ህዳር 4 ቀን 2019 ዓ.ም) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወይዘሮ ያስሚን ወሀብረቢ ከፓኪስታን የንግድ ሚኒስትር ክቡር ጃም ካማል ኻን ጋር የሁለቱን ሀገራት የንግድ ትስስር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በበይነ-መረብ (Virtual) ፍሬያማ ውይይት አካሂደዋል።
በውይይቱ ወቅት ክብርት ሚኒስትሯ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እና እያደገ የመጣውን የንግድ ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ኢትዮጵያ ያላትን ጽኑ ቁርጠኝነት ገልጸዋል። ክብርት ወይዘሮ ያስሚን አክለውም እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2023 በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈረመው የንግድ ስምምነት በተሟላ መልኩ ወደ ስራ ስለሚገባበት ሁኔታም መክረዋል።
የፓኪስታን እስላማዊ ሪፐብሊክ የንግድ ሚኒስትር ክቡር ጃም ካማል ኻን በበኩላቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ሁለንተናዊ ትብብርና አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር ሀገራቸው ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።
የሁለቱም ሀገራት የቴክኒክ ኮሚቴ እና የጋራ ኮሚሽን በቅርብ ጊዜ ውስጥ በመገናኘት የሀገራቱ የንግድ ግንኙነት በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ በጋራ የሚሰሩ ይሆናል።